የደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መልዕክት

ምክር ቤቶች የህዝብ ሉዓላዊነት መገለጫ፣ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እምብርትና የዴሞክራሲያዊ አገዛዝ አውራ ተቋሞች ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት የህዝቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የማረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት በየምርጫ ዘመኑ በተወከሉ የህዝብ እንደራሴዎቹ አማካይነት በህገ-መንግስቱና በመረጠው ህዝብ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በመወጣት እየሰራ ይገኛል፡፡ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ ህግ ማውጣት ሲሆን ሌላው የአስፈፃሚውን አካል የሥራ አፈጻጸም ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የህዝብ ውክልናን መወጣት ነው፡፡ በመሆኑም ባለፉት የምክር ቤቱ የሥራ ዘመንም ዛሬም የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ ይገኛል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት የክልሉን ህዝብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል በየበጀት አመቱ የሚከናወኑ ተግባራትን አፈጻጸምና በየጊዜው የሚወጡ ሕጎች ተግባራዊ መሆናቸውን ባደራጃቸው ቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን በማከናወን በክልሉ የዴሞክራሲ፤ የልማትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ላይ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡ ቋሚ ኮሚቴዎች በምክር ቤቱ የወጡ ህጎች ተግባራዊ ስለመደረጋቸው፣ የፀደቁ ዕቅዶች በየደረጃው ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረጋቸው፣ የፀደቀው በጀት ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ መዋሉን አስፈፃሚውን አካል ጠርተው ይወያያሉ፡፡ በመስክ እስከ ቀበሌ በመውረድ ምልከታ በማድረግ እና የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ለታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ግብረ መልስ ይሰጣሉ፡፡ የክልሉን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በክልሉ እየመጣ ካለው ልማት እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በሚከናወኑ የልማት ተግባራት አፈጻጸም ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ብልሹ አሰራርና ኪራይ ሰብሳቢነትን ከመታገል አንጻር ተገቢዉን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችን በተለይም ሰፊ የህዝብ ቁጥር የሚገኝባቸዉን የቀበሌ ምክር ቤቶች ለማጠናከር የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ በሌላም በኩል ድጋፍና ክትትል በማድረግ ግብረ መልስ በመስጠት የየምክር ቤቶቹን አፈፃፀም የማጠናከር ሥራም በምክር ይከናወናሉ::