የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 178/2011

የክልላችንን የኢኮኖሚ ዕድገት በላቀ ደረጃ ለማፋጠን ይቻል ዘንድ የአስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት የተልዕኳቸውን ስፋትና ተቀራራቢነት መሰረት ባደረገ መልኩ እንደገና መወሰን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፣ በተሻሻለው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሕገ-መንግስት አንቀፅ 51 ንዑስ አንቀፅ 3 (ሀ) መሰረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

 

ክፍል አንድ

 

ጠቅላላ

 

1. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ “የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር 178/2011” ብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ ፡-

1) ክልል” ማለት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ነው፡፡

2) ክልል ምክር ቤት” ማለት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል

መንግሥት ምክር ቤት ነው፡፡

3) “መስተዳድር ምክር ቤት” ማለት በተሻሻለው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና

ሕዝቦች ክልል ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 65 መሠረት የተገለጸው ሆኖ በዚህ አዋጅ

አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተው ከፍተኛ የአስፈፃሚ አካል ወይም ካቢኔ

ነው፡፡

4) “አስተዳደር ምክር ቤት” ማለት እንደአግባብነቱ የዞን፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣የልዩ ወረዳ፣ የወረዳ አስተዳደር አስፈፃሚ አካል ወይም ካቢኔ ነው፡፡

5) “አስተዳደር እርከን” ለት እንደአግባብነቱ በክልሉ የሚገኙ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣የወረዳ፣ የከተማ፣ የክፍለ ከተማ እና የገጠርና ከተማ ቀበሌ አስተዳደርን ያጠቃልላል፡፡

6) “የአስፈፃሚ አካላት መሥሪያ ቤት” ማለት ቢሮ፣ ኮሚሽን፣ ኤጀንሲ፣ ኢንስቲቲዩት፣ጽሕፈት ቤት፣ ባለስልጣን መሥሪያ ቤት እና ሌሎች የመንግሥት አስተዳደር

ተግባር ለማከናወን በዚህ አዋጅና በሌሎች ሕጐች መሰረት የተቋቋሙትንና በሥራቸው ያሉትን መሥሪያ ቤቶችን ያጠቃልላል፡፡

7) “ቢሮ” ማለት ለመስተዳደር ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑ የክልሉ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ናቸው፡፡

8) “ኃላፊ ወይም ምክትል ኃላፊ” ማለት እንደቅደም ተከተሉ የአስፈፃሚ አካላት መሥሪያ ቤቶችን በበላይነት ለመምራት በኃላፊነት የተሾመ ወይም የተመደበ ኃላፊ ወይም ምክትል ኃላፊ ነው፡፡

9) “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፡፡