የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ውጤታማ ለማድረግ በልዩ ትኩረት ሊሰራ ይገባል።

ይህ የተገለጸው የክልሉ ምክር ቤት የሥርዓተ ፆታና ህፃናት ማካተት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ደጋፊ የሥራ ሂደት ለምክር ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች በኤች አይ ቪ ኤድስ ወቅታዊ ጉዳይ፣ በማህፀን በር ካንሰርና በጡት ካንሰር እና በስርዓተ ፆታ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሰጠበት ወቅት ነው። በስልጠናውም የኤች አይ ቪ ኤድስ አጠቃላይ ሁኔታ፣ የማህጸን በርና የጡት ካንሰር በተመለከተ ወ/ሮ ፀሐይ አየለ በክልሉ ጤና ቢሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል አስተባባሪ፣ ስርዓተ ፆታን በተመለከተ ወ/ሮ አበበች እልታሞ ከክልሉ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ሴቶች ህፃናት ማካተት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ዳይ/ዳይሬክተር ሰነዶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። ከተሳታፊዎችም የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የተቀዛቀዘውን የኤች አይ ቪ ኤድስ ጉዳይ በልዩ ትኩረት ከዚህ ቀደም በነበረው ግለት በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባም አንስተዋል። የሴት እህቶቻችንን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘውንና በአስፈሪ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለውን የማህፀንና የጡት ካንሰር ለመከላከል ብሎም ከተከሰተም በኃላ አስፈላጊውን ህክምና በመከታተል መዳን እንደሚቻል ግንዛቤ እንዳገኙ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ከማጠናከር አንፃር የተሠሩ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም በሚፈለገው ልክ ውጤት ባለመመዝገቡ በመቀናጀት በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባም የስልጠናው ተሳታፊዎች አንስተዋል። የምክር ቤቱ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አማሩ ሀቱዬ መድረኩን ሲያጠቃልሉም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መንስኤና መከላከያ መንገዶችን በመለየት ጤናችንን ለመጠበቅ አቅም የሚፈጥር ስልጠና መሆኑን አንስተዋል። ኤች አይ ቪ ኤድስንና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ለማስቀረት በቅንጅት መስራት አለብን ብለዋል አቶ አማሩ። የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ እንደ ምክር ቤት ሰፊ ስራዎች ታቅደው እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸዋል። የሴክተር መስሪያ ቤቶች ዕቅድ የሴቶች ተጠቃሚነትን ስለማካተታቸው፣ ተግባራዊነቱንም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከመገምገም ባሻገር በአካል ውጤታማነቱ እየተፈተሸ መሆኑን ጠቁመው ከመጣንበት ውስብስብ ችግር አንጻር ቀሪ ተግባር ላይ ተከታታይ ንቅናቄ ማድረግ አለብን ብለዋል። የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት የአመራሩና የባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት እጅግ ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ ውይይቱ ተጠናቋል።