ለተቋማት ውጤታማነት

መጋቢት 30/2014 ለተቋማት ውጤታማነት ተናቦና ተቀናጅቶ መሥራት ወሳኝ ነው፦ የተከበሩ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞል የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ_ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ይህን የተናገሩት የምክር ቤቱ የ9 ወራት የዕቅድ አፈጸፃም ሪፓርት በአስተባባሪ ደረጃ በተገመገመበት ወቅት ነው። የደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወራት የእቅድ አፈጻፀም ሪፖርት የምክር ቤቱ አስተባባሪና ማኔጅሜንት አካላት በተገኙበት ተገምግሟል። ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን ካቀዳቸው ተግባራት መካከል መደበኛና አስቸኳይ ጉባኤዎችን ማካሄድ፣ የቋሚ ኮሚቴዎች የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችና የለውጥ ስራዎች በአመዛኙ በጠንካራ ጎኑ የተገመገሙ ናቸው። በሌላ መልኩ ታቅደው ያልተከናወኑ ተግባራት መካከል የህዝብ አስተያየት መድረኮች፣ የምክር ቤቶች የጋራ መድረክ፣ ታችኞቹን ምክር ቤቶች ድጋፍ ያለማድረግ ተጠቃሽ ሲሆኑ በቀጣይ ሩብ ዓመት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚከናወኑም ነው የተነሳው። ከመልካም አስተዳደር አንጻር አንዳንድ የስራ ክፍሎች ፈጣን አገልግሎት ያለመስጠት፣ ግዥ በወቅቱ ጥራተቸውን ጠብቀው ያለመገዛት፣ በደረጃ ዕድገትና ዝውውር ላይ የሚታዩ ክፍተቶች መታረም እንዳለባቸውም አስተባባሪ ኮሚቴ ገምግሟል። በማጠቃለያም የተከበሩ ወ/ሮ ፋጤ እንዳነሱት በቀሪ ጊዜያት ሊሳኩ የሚችሉ ተግባራትን ለይቶ አመራሩና ፈፃሚው ተናቦ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል።